እንኳን ወደ ኢንዱስትሪ ሚ/ር በሰላም መጡ

የክቡር አቶ አህመድ አብተው

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር መልዕክት

አገራችን ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ጎራ ለመቀላቀል ብሎም ወደ ብልጽግና የእድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ የምትችለው በዓለም ዓቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪ ስትገነባ ነው፡፡ ይህንኑ ለማረጋገጥ ባለፋት ተከታታይ ዓመታት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት በተከናወኑ ተግባራት ከፍተኛ ለውጦች በመመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡

በተያያዝነው የህዳሴ ጉዞ ከግብ ለማድረስና የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ግቦቻችንን ለማሳካት በተደራጀ የልማት ሠራዊት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የሠራዊቱን ክንፎች በአመለካከት ለማቀራረብ፣ ክህሎቶቻቸውን ለማሻሻል፣ አደረጃጀቶችንና አሠራሮችን ለማጠናከር በተከናወኑ ሥራዎች አመርቂ ውጤቶችን ማየት የተጀመረባቸው ከተግባራዊ እንቅስቃሴም በርካታ ልምዶችን የተቀሰመባቸው ከመሆናቸው በላይ በቀጣይም የላቀ አፈፃፀም ለማስመዝገብ አቅም የፈጠርንባቸው ሆነዋል፡፡ የ2007 በጀት ዓመት የመጀመሪያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማጠቃለያ እንደመሆኑ መጠን በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ልማት ዘርፍ የተያያዝነውን ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳለጥ ከፍተኛ ድርሻ ስላለው ግቡን ለማሳካት ሁለንተናዊ ጥረትና ርብርብ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ ለበለጠ

ዜና

የኢንዱስትሪ ፓርክ በአካባቢና በህብረተሰቡ ላይ በሚያደርሰው ተፅዕኖ ዙሪያ ጥናታዊ ውይይት ተካሄደ
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር UNOPS የተባለ አለም አቀፍ ድርጅት የኢንዱስትሪ ፓርክ የአካባቢና የህብረተሰብ ተፅዕኖ ዙሪያ ያስጠናውን ጥናት በ27/10/2009 በሂልተን ሆቴል የሚመለከታቸውን ባላድርሻ አካላት አወያየ፡፡
በውይይቱ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን፣ የከተማ ልማት ሚኒስቴር፣ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣የደንና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ከአማራ፣ ደቡብና ኦሮሚያ ኢንዱስትሪና አካባቢ ጥበቃ ቢሮዎች እንዲሁም ከሌሎች አጋር ድርጅቶች የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ 
ከUNOPS በመጡ ባለሙያዎች የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ በአካባቢ ማለትም ከአየር ንብረት ፣ከአካባቢያዊ አቀማመጥ፣ ከአፈርና ውሃ አኳያ እንዲሁም በአካባቢው ህብረተሰብ ላይ ከሚያመጣው የባህል ፣የመልሶ ማቋቋምና የመሰረተ ልማት ማለትም የጤናና የንፁህ ውሃ አቅርቦት አንፃር የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በመተንተን አቅርበዋል፡፡
ከደቡብና አማራ ክልል የመጡ የውይይቱ ተሳታፊዎች በኢንዱስትሪ ፓርኩ ለሚነሱ የህብረተሰብ ክፍሎች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው የመልሶ ማቋቋም ጽ/ቤት በመክፈት እየሰሩ መሆኑንና የተመረጡ አካባቢዎችም በጥናት የተለዩና ከፍተኛ ክትትል የሚደረግባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር መብራህቱ መለስ በበኩላቸው ኢንዱስትሪ ፓርክን በማስፋፋት አካባቢያዊና ማህበረሰባዊ ተፅዕኖ የማያደርስ መሆኑን በተጠናው የጥናት ሰነድ ከሚመለከታቸው አለም አቀፍ ተቋማት የእውቅና ሰርቲፍኬት መገኘቱን በመግለጽ ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ የአካባቢና የማህበረሰብ ተፅዕኖ የሚከታተል ቡድን መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡

የአገር ውስጥ ባለሃብቶች የንቅናቄ መድረክ ተካሄደ

መንግስት የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በማምረቻው ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግና በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶ እያደረገ ያለውን ድጋፍ ለማስተዋወቅ በ26/10/2009 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል፡፡ በንቅናቄው በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶችና የሚመለከታቸው የመንግስት ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ልማት ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ እንደገለፁት መንግስት የሀገራችንን እድገት ለማፋጠን ከዚህ በፊት ለትምህርት፣ለጤናና ለመሰረተ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት ሲሰራ የቆየ ሲሆን በአሁኑ በወቅት ግን ያለ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ለውጥ የማይታሰብ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ገልጸዋል ፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለሚሰማሩ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች መንግስት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር በመተባበር የሊዝ ፋይናንሲንግ ስርዓት አመቻችቷል ብለዋል ፡፡ ባለሃብቱ በማምረቻው ዘርፍ በመሳተፍ የትራንስፎርሜሽኑ ስኬት ባለቤት በመሆን መንግስት ያመቻቸውን ማበረታቻ በመጠቀም አዋጭ በሆኑ የስራ መስኮች እንዲሳተፉ አሳስበዋል፡፡ 
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ተሾመ አለማየሁ በበኩላቸው ተቋሙ ከመንግስት በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት በማምረቻው ዘርፍ የሚሰማሩ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን ለመደገፍ በጀት መድቦ እየሰራ ነው፡፡ በ2009 በጀት ዓመት የተመደበው 7.5 ቢሊዮን ብር ቢሆንም በሊዝ ፋይናንስ የሚገዙት ለማምረቻው ዘርፍ የሚያገለግሉ ማሽኖች በሃገር ውስጥ ባለመመረታቸውና ወደ ዘርፉ የሚገቡት የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች አናሳ መሆንና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ከተመደበው ብር ውስጥ ተግባር ላይ የዋለው 2 ቢሊዮኑ ብር ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 
የመድረኩ ተሳታፊ የነበሩት ባለሀብት አቶ ምኒልክ ተስፋዬ እንደገለፁት መንግስት የማምረቻውን ዘርፍ ለማሳደግ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አድንቀው ወደ ዘርፉ የሚቀላቀሉ ባለኃብቶችን ተስፋ የሚያስቆርጡ ቢሮክራሲያዊ አሰራሮች ጊዜ ሳይሰጣቸው ሊስተካከሉ ይገባል ብለዋል፡፡

 

ፐብሊክ ሰርቪሱ ለሀገር ህዳሴ እውን መሆን በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት ተገለፀ

የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሰራተኞችና አመራሮች 11ኛውን የፐብሊክ ሰርቪስ ቀን ሰኔ 22 ቀን 2009 ዓ.ም ባከበሩበት ወቅት እንደተገለፀው ፐብሊክ ሰርቪሱ 12ቱን የስነምግባር መርሆዎች በአግባቡ ተረድቶ የተሰማራበትን ስራ በአግባቡ ከተወጣ ለሀገር ህዳሴ መረጋገጥ ሚናው የላቀ እንደሆነ ተገለፀ፡፡
በዕለቱ በሥነ-ምግባሩ የተመሰገነ ፐብሊክ ሰርቪስ ለኢትዮጵያ ህዳሴ የሚል ሰነድ የቀረበ ሲሆን ባለፉት 25 ዓመታት ያስመዘገባቸውን ድሎችና መሻሻል በሚገባቸው አሰራሮች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የቆዳና ጨርቃጨርቅ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ቦጋለ ፈለቀ የመልካም አስተዳደር መስፈን የሚረጋገጠው በፐብሊክ ሰርቪሱ የተቀላጠፈ አገልግሎት መሆኑን በመገንዘብ ሀገራችንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ የበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
አክለውም ሁሉም የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኛ የያገባኛልና የአገልጋይነት ስሜትን በመላበስ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥሩ የበላይ አመራሮችንና ባለሙያዎችን በመታገል የአምራች ዘርፉ የተቀላጠፈ የስራ እንቅስቃሴና አፈፃጸም ዋና ተዋናይ መሆን ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ 
ሰራተኞችም በበኩላቸው ማገልገል ክብር ነው! ድህነትን ለማሸነፍ ማገልገል ደግሞ ድርብ ክብር ነው! የሚለውን መፈክር በልባችን በማተም ለለውጥ በትጋት እንሰራለን በማለት ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች በበላይ አመራሩ ምላሽ በመስጠት የበዓሉ አከባበር ተጠናቋል፡፡