እንኳን ወደ ኢንዱስትሪ ሚ/ር በሰላም መጡ

የክቡር አቶ አህመድ አብተው

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር መልዕክት

አገራችን ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ጎራ ለመቀላቀል ብሎም ወደ ብልጽግና የእድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ የምትችለው በዓለም ዓቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪ ስትገነባ ነው፡፡ ይህንኑ ለማረጋገጥ ባለፋት ተከታታይ ዓመታት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት በተከናወኑ ተግባራት ከፍተኛ ለውጦች በመመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡

በተያያዝነው የህዳሴ ጉዞ ከግብ ለማድረስና የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ግቦቻችንን ለማሳካት በተደራጀ የልማት ሠራዊት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የሠራዊቱን ክንፎች በአመለካከት ለማቀራረብ፣ ክህሎቶቻቸውን ለማሻሻል፣ አደረጃጀቶችንና አሠራሮችን ለማጠናከር በተከናወኑ ሥራዎች አመርቂ ውጤቶችን ማየት የተጀመረባቸው ከተግባራዊ እንቅስቃሴም በርካታ ልምዶችን የተቀሰመባቸው ከመሆናቸው በላይ በቀጣይም የላቀ አፈፃፀም ለማስመዝገብ አቅም የፈጠርንባቸው ሆነዋል፡፡ የ2007 በጀት ዓመት የመጀመሪያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማጠቃለያ እንደመሆኑ መጠን በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ልማት ዘርፍ የተያያዝነውን ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳለጥ ከፍተኛ ድርሻ ስላለው ግቡን ለማሳካት ሁለንተናዊ ጥረትና ርብርብ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ ለበለጠ

ዜና

በአልሚ ምግብ ማበልፀግ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ

ሀገራዊ  የአልሚ  ምግብ ማበልፀጊያ ውይይት ነሐሴ 15 ቀን 2009 ዓ.ም በሀርመኒ ሆቴል ተካሄደ፡፡ ውይይቱ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአግሮ ፐሮሰሲንግ ዘርፍ የተዘጋጀ ነው፡፡በውይይቱ ላይ ምግብ ማበልጸግ ማለት ለሰው ልጅ ጤንነት ጠቃሚ የሆኑ ቫይታሚኖችንና ሚኒራሎችን በምግብ ውስጥ በመጨመር በስርዓተ ምግብ መዛባት የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን በማስወገድ አምራችና ጤናማ ህብረተሰብ መፍጠር ማለት ነው፡፡በኢትዮጵያ ጤና ኢንስቲትዩት በ2001 ዓ.ም በተደረገው ጥናት የተመጣጠነ የስርዓተ ምግብ እጥረት በትምህርት፤ በምርታማነትና በጤና ላይ በሀገሪቱ ያደረሰው ዓመታዊ አጠቃላይ ኪሳራ 55.5 ቢሊዮን ብር እንደሆነ የተገመተ ሲሆን ይህም የሀገሪቷን አጠቃላይ ገቢ 16.5 በመቶ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ 
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር መብራህቱ መለስ ዉይይቱን በከፈቱበት ወቅት ጥራቱን የጠበቀና የተመጣጠነ ምግብ የማበልጸግ ስራ በአካል እና በአእምሮ የዳበረ አምራች ማህበረሰብ እንዲፈጠር ያስችለናል ብለዋል፡፡
አክለውም ቀጣዩ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አቅጣጫ ከግሉ ሴክተር ጋር በመቀናጀት በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የሚገቡትን አልሚ ምግቦችን በሀገር ውስጥ ማምረት ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም የሀገር ዉስጥ የዘይት ፋብሪካዎች የሚያመርቱትን ዘይት በቫይታሚን ኤ እና ዲ በሚፈለገው መጠን በማበልጸግ እንዲሁም የአይረንና የዚንክ ንጥረ ነገሮች የስንዴ ዱቄት በሚያመርቱ ፋብሪካዎች ላይ በሚፈለገው ስታንዳርድ በማበልጸግና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ እየደረሰ ያለውን የጤናና ምርታማነት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡


ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በ2010 ዓ.ም ስታንዳርድ የተዘጋጀ መሆኑንና በ13 የስንዴ ዱቄት ፋብሪካዎችና በ2 የዘይት ፋብሪካዎች የሙከራ ትግበራ እንደሚጀምርና በቀጣይም በሁሉም ፋብሪካዎች ምግብን በቫይታሚን የማበልጸግ ስራ ተግባራዊ እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡ 
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በማምረቱ ሂደት ውስጥ በዋነኝነት ከሚያጋጥሙ ችግሮች መካከል የተቀናጀ የአሰራር ክፍተት፣ የአቅም ግንባታ ክፍተት፣የላባራቶሪ መሳሪያዎች አለመሟላት፣ ተግባብቶ አለመስራትና ግንዛቤ አለመፍጠር ዋናዋናዎቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡  በውይይቱ ላይ የ13 የተለያዩ ምግብ ማበልጸጊያ ፋብሪካ ኃላፊዎችና እና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ተገኝተዋል፡፡

በስጋና ወተት ምርት መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ላይ ውይይት ተካሄደ

የኢትዮጵያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከመጡ ባለድርሻ አካላት ጋር ነሀሴ 12 ቀን 2009 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል በንዑስ ዘርፉ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡  በውይይቱ ላይ በንዑስ ዘርፉ ያለውን መልካም አጋጣሚና የኢንዱስትሪ ክላስተር አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ጽሑፍ ያቀረቡት በኢንስቲትዩቱ የኢንቨስትመንትና ምግብ ፓርኮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ካሳ ሲሆኑ በሀገሪቱ ከ300 በላይ ቄራዎች ያሉ ሲሆን ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩንም አብራርተዋል ፡፡አያይዘውም በ13 ቄራዎች ብቻ 467 ወንዶችና ከ80 በላይ ሴቶች የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡
በመቀጠልም የዘርፉን የግብዓት አቅርቦት ችግርና በንዑስ ዘርፉ ላይ ያለውን ተስፋ በተመለከተ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት በኢትዮጵያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የገበያ ልማት ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ መኮንን ጋሹ ናቸው፡፡  አቶ መኮነን ለውይይት ባቀረቡት ጽሑፍ የ2009 ዕቅድ አፈፃፀም ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት ለገበያ የሚቀርቡ እንስሳት መስፈርት አለማሟላት፡ጥራት፡ በዋጋ ተወዳዳሪ መሆን አለመቻል እንደሆነ አስቀምጠዋል፡፡


በ2010 በጀት ዓመት ዕቅዱን ለማሳካት የትራንስፖርት አቅርቦት ማመቻቸት፤ተደጋጋሚ ቀረጥ ማስቀረት፤የኮንትሮባንድ ንግድን መቀነስ፤የማቆያ ቦታን ማመቻቸትና ገበያን ማበረታታት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡ አክለውም ወደ ስራ የሚገባው አላና ፋብሪካ በቀን 3000 ከብትና 6000 በግና ፍየል ስለሚፈልግ እጥረት እንዳይገጥመው ጥረት ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡  በዕለቱ ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ የሰጡት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር መብራህቱ መለስ ሲሆኑ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እያጋጠመን ያለው ችግር የሀይል እጥረት ሳይሆን የትራንፎርመሮች ማርጀት በመሆኑ በአዲስ ለመተካት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጋር ስምምነት ተፈራረመ

የስምምነቱ ዓላማ በጨርቃጨርቅ ዘርፍ የሴቶችንና ወጣቶችን አቅም ለመገንባት ሲሆን የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅትን በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት በኢትዮጵያ የዩኒዶ ተወካይ እና ዳይሬክተር ሚስተር ጉስታቮ አሼምበርግ ናቸው፡፡  ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪውን ክፍለ-ኢኮኖሚ ለማዘመን የምታደርገውን እንቅስቃሴ አድንቀው የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ሀገራት ጋር በመስራቱ ደስተኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ አክለውም የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለዚህ ፕሮጀክት ትግበራ 2.5 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የጨርቃጨርቅና ቆዳ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ቦጋለ ፈለቀ ናቸው፡፡   ሚኒስትር ዴኤታው ስምምነቱን በፈረሙበት ወቅት የፕሮጀክቱ በፍጥነት ወደ ስራ መግባት እንዳስደሰታቸውና ይህ ስምምነት የሴቶችንና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር በአሁኑ ወቅት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የሚስተዋለውን የዜጎች ፍልሰት ለመቀነስ የተደረገው ስምምነት ሚናው የጎላ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

ለፕሮጀክቱ ትግበራ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እና የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የተመረጡ ሲሆን ፕሮጀክቱ የ3 ዓመታት ቆይታ እንደሚኖረውም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የዘርፍ ማህበራት ም/ቤት አባላት የማስተካከያ ምርጫ ተካሄደ

ምክር ቤቱ በነሃሴ 2008 ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ የምክር ቤቱን አባላት የመረጠ ቢሆንም የተደረገው ምርጫ የማህበሩን መተዳደሪያ ደንብ የተከተለ ባለመሆኑ ከማህበሩ አባላት በተነሳው ጥያቄ መሰረት ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ከዘርፍ ማህበሩ የተወጣጣ ኮሚቴ ባደረገው ምርመራ ምርጫው የህግ ስህተት እንደነበረበት በመረዳቱ ምርጫው ድጋሜ እንዲካሄድ ተደርጓል ሲሉ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የህግ አገልጎሎት ዳይሬተሩ አቶ ተካልኝ ከድር ገልጸዋል፡፡ በተፈጠረው የህግ ስህተት ምክንያት የማስተካከያ ምርጫ ለማድረግ እንዳስፈለገም ዳይሬክተሩ አክለው ተናግረዋል ፡፡

አንዳንድ የዘርፍ ምክር ቤት አባላት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ቢዘገይም ኮሚቴ አቋቁሞ ጉዳዩ እንዲጣራ ማድረጉና ለማስተካከያ ምርጫው ሁኔታዎችን ማመቻቸቱ ሊያስመሰግነው ይገባል ብለዋል፡፡ ለወደፊቱ በማህበሩ መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል ፡፡
 

 

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የብረታ ብረትና ኬሚካል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አለሙ ስሜ በበኩላቸው ማህበሩ ነጻ ማህበር በመሆኑ የራሱን ህገ ደንብ የማውጣትና ባወጣው ህገ ደንብ የመተዳደር መብት አለው፡፡ ባወጣው ህገ ደንብ የመተዳዳር ግዴታም አለበት ብለዋል፡፡ ሆኖም ግን የማህበሩም ሆነ የመንግስት ህግና ድንብ ሲጣስ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዝም ብሎ የሚያይበት ምክንያት የለም ብለዋል ፡፡
በመጨረሻም በማህበሩ ህገ ደንብ መሰረት አዳዲስ የቦርድ አባላት፣ የማህበሩ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ተመርጠዋል፡፡ የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ እያሱ ሞሲሳ ምክትል ፕሬዚዳንት ደግሞ አቶ ልሳኑ በለጠ ሆነው ተመርጠዋል ፡፡